ፓርቲዎቹ ያለፉትን አምስት ዓመታት አስመልክቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቀረበው ንግግር ዙሪያ ሀሳባቸውን ለአሐዱ የሰጡ ሲሆን፤ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይም ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በፓርቲው ምስረታ አምስተኛ ዓመት የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር፤ "ባለፉት አምስት ዓመታት ብልፅግና ያሳካቸው ድሎች ታፈሰው የማያልቁ ናቸው" ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

Post image

ያለፉትን አምስት ዓመታት የኢኮኖሚ ጉዞ በሚመለከት ሀሳባቸውን ለአሐዱ ያጋሩት የእናት ፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አስፋ አዳነ፤ እናት ፓርቲ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከመንግሥት በተቃራኒ መልኩ እንደሚመለከተው ተናግረዋል፡፡

"የመንግሥት ተቀዳሚ ሥራ መሆን ያለበት የዜጋው በሰላም ወጥቶ መግባት ነው" የሚሉት ዶክተር አሰፋ፤ "ዜጋው ግብር የሚከፍለው መሰረተ ልማት እንዲሟላለትና በሰላም ወጥቶ ለመግባት ነው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የኢኮኖሚ ዕደገት አለ ብሎ ማሰብ ተገቢ አይደለም" ብለዋል፡፡

"ኢኮኖሚው ከሚገባው በላይ የመውደቅ አደጋ የተጋረጠበት ሆኖ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተርበው መመገብ የተሳናቸው እና ሌሎች በርካታ የሚነሱ ጉዳዮች ባሉበት በዚህ ጊዜ ስለ ኢኮኖሚ ዕደገት መነጋገር ተገቢ አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

"በተደጋጋሚ ባለፉት አምስት ዓመታት ዕድገት መመዝገቡ በተለያየ አጋጣሚ ሲገልጽ ቆይቷል" ያሉም ሲሆን፤ ነገር ግን ለህብረተሰቡ እዚህ ግባ የሚባል ነገር ያልታየበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የህብረተሰቡን ቅድሚያ የሚሰጠውን ጉዳይ ችላ በማለት የሚፈልገውን ጉዳይ ብቻ እየሠራ እንደሆነም፤ ዶክተር አሰፋ ከአሐዱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

በብፅግና ፓርቲ ምስረታ ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ንግግር ያደረጉት የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ በተለይም በፖለቲካ ምህዳሩ ዙሪያ እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በተያያዘ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ "ያለፉትን አምስት ዓመታት ከቃላት በዘለለ ይህ ነው የሚባል ግጭት ውስጥ አልገባንም" ብለዋል፡፡

ይህንን በሚመለከት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሙላት ገመቹ ሲገልጽ፤ "ከሶማሊያ ጋር ያለው ግንኙነት በሚታወቅበት ሁኔታ ላይ ሆነን እንዲሁም ከተለያዩ የሀገሪቱ ድንበሮች ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ በሆንበት ጊዜ ላይ 'ምንም ግጭት የለም' ብሎ መግለጽ ተገቢ አይደለም" ይላሉ፡፡

ዓለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ድንበር መከበር አለበት የሚሉትና ሀሳባቸውን ለአሐዱ የሰጡት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ፤ "በድንበር አካባቢ የሚገኙ የሀገሪቱ ይዞታዎች በወራሪዎች እጅ ባለበት ሁኔታ ሰላማዊ ግንኙነት ውስጥ ነው ያለነው የሚል ሀሳብ ተቀባይነት የለውም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

"ከሁሉም በላይ ግን ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት 'አሳክቼዋለው' ካለው የውጭ ጉዳይ አስቀድሞ በውስጥ ያሉ ችግሮችን ሊፈታ ይገባል" ሲሉም አክለዋል፡፡

በፓርቲው አምስተኛ ዓመት ምስረታ ማጠቃላይ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ብልፅግና ፓርቲ በቀጣይ አምስት ዓመታት ከአሁኑ በላቀ አዳዲስ ድሎችን ያስመዘግባል" ሲሉ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡