ታሕሳስ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዳግም ምዝገባ እንዲያካሄዱ ጥሪ ቀርቦላቸው ምዝገባ ባላካሄዱ 84 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡

የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ማርታ አድማሱ፤ ወጥነት ያለው የፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት እንዲተገበር የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳግም ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን ለኤፍ ኤም ሲተናግረዋል

በዳግም ምዝገባውም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ የተሳሳተ ሰነድ ካላቸው እንዲያስተካክሉ አልያም የጎደለውን እንዲያሟሉ እድል ተሰጥቷቸው እንደነበርም ተናግረዋል

ዳግም ምዝገባ እንዲያደርጉ ጥሪ ከቀረበላቸው 102 ተቋማት ውስጥም 84 የሚሆኑት ዳግም ምዝገባ አለማድረጋቸውን ገልጸው፤ "ምዝገባ ያላከናወነ ተቋም በራሱ ፈቃድ ከመማር ማስተማር ሥራው እንደወጣ ይቆጠራል" ብለዋል።

እነዚህ ተቋማትም ከመማር ማስተማር ሥራው ሲወጡ የመውጫ ፎርም እንዲሞሉ የሁለት ሳምንት ጊዜ ገደብ እንደተሰጣቸውም የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል።

አሁን ላይ አምስት ተቋማት ብቻ ይህንን ሂደት የጀመሩ ሲሆን፤ ወደዚህ ሥራ ያልገቡ ቀሪ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ በፍታብሄር እና በወንጀል ሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

ተቋማቱ ከዚህ በኋላ በሰነድ የታገዘ ምዝገባ እንደማያደርጉ እና ዳግም ወደ መማር ማስተማር ሥራው እንደማይመለሱም አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይም ዘጠኝ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ተመሳሳይ ርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸው፤ በተቋማቱ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች አስፈላጊውን መረጃ በማሟላት እስከ ጥር ወር 2017ዓ.ም መጀመሪያ ድረስ ፈቃድ ወዳላቸው ተቋማት እንዲያዛውሩ ትዕዛዝ መሰጠቱንም አስረድተዋል፡፡