መጋቢት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የታላቁ የህዳሴ ግድብ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅና ቀሪ ተርባይኖች ሀይል እንዲያመነጩ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቋል፡፡

ግንባታው ከ97 ነጥብ 6 በመቶ በላይ እንደደረሰና ጥቂት የማጠናቀቂያ ሥራዎች ብቻ እንደቀሩት ፅህፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚንስቴር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ "ቢበዛ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሪቫን በጋራ እንቆርጣለን!" ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

በዚህም ግድቡን በስድስት ወራት ዉስጥ ለማጠናቀቅ የቴክኒክ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንና ወደ ሥራ ያልገቡ ዩኒቶችም ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ፤ የጽህፈት ቤቱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን ዳንኤል ለአሐዱ ገልጸዋል።

Post image

አክለውም ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ እስካሁን በቦንድ ግዢ እና በሌሎች የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች በሰባት ወራት ውስጥ ብቻ 780 ሚሊዮን ብር በላይ ስለመሰብሰቡ አንስተው በአጠቃላይ ግን እስከአሁን 21 ቢሊዮን 666 ሚሊዮን ብር መሠብሰቡን ተናግረዋል፡፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 5 ሺሔ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ያመላከተው ጽህፈት ቤቱ፤ ዓመታዊ የኃይል ምርቱ ደግሞ 15 ሺሕ 760 ጊጋ ዋት ይሆናል መባሉን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የግንባታው የመሠረት ድንጋይ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመጋቢት 24 ቀን 2003 የተጣለው የሕዳሴው ግድብ 14 ዓመት ሊሞላው የተቃረበ ሲሆን፤ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር 5 ሺሕ 250 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳለው ተነግሮ እንደነበርም የሚታወስ ነው።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ