ጥር 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት እንደልብ ተንቀሳቅሶ ኩነቶችን ለመመዝገብ ተግዳሮት እንደሆነበት የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

የመረጃ ምንጭ ከመሆን አንፃር ኩነቶችን በሁሉም አካባቢዎች ለመመዝገብ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት የአገልግሎቱ የእቅድ በጀት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር ዋለ ቅዱሱ፤ በታቀደው መንገድ ለመስራትና ተንቀሳቅሶ ለመመዝገብ በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይም በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎች ካለው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የወደሙ ንብረቶች፣ ኮምፒውተሮችና የምስክር ወረቀቶች የመሳሰሉትን መልሶ ለማደራጀት የግብዓት እጥረት መኖሩን በማንሳት፤ ይህም በምዝገባ ስርዓቱ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።

የበጀት እጥረትም ሌላኛው በክልሉ ኩነቶችን ለመመዝገብ ተግዳሮት የሆነ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ሥራ በሚሰራባቸው የቀበሌ ጣቢያዎች ላይ ራሱን የቻለ የምዝገባ ባለሙያ አለመኖሩም ክፍተት የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል።

በመሆኑም በተለያየ መንገድ የግንዛቤ ማስጠበጫ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ በመጥቀስ፤ በ2017 በጀት ዓመት በ5 ወራት ውስጥ ከ526 ሺሕ በላይ የተለያዩ ወሳኝ ኩነቶችን ለመመዝገብ ታቅዶ 209 ሺሕ 22 መመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል።

ይህም ከተያዘው እቅድ ግማሽ በታች 39 ነጥብ 7 ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት በ5 ወር ውስጥ ከ68 ሺሕ በላይ ሞት ለመመዝገብ ታቅዶ 14 ሺሕ 535 መመዝገብ መቻሉን ለአሐዱ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል 179 ሺሕ 625 ልደት፣ 14 ሺሕ 97 ጋብቻ፣ 752 ፍቺ እና 11 ጉዲፈቻ ምዝገባ መከናወኑንም ጠቅሰዋል።

በክልሉ ለሚገኙ የተለያየ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከተፈጠረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የተመዘገበው ኩነት አነስተኛ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ዋናው ተግዳሮት የሰላም እጦት መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ