ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በአክሱም ሙስሊም ተማሪዎች ላይ ከሂጃብ ክልከላ ጋር ተያይዞ ፍርድ ቤት እና የትምህርት ቢሮ የተሰጠው ወሳኔና ትዕዛዝ እንዲተገበር የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በዛሬው ዕለት በመቀሌ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ምክር ቤቱ "ሂጃቧን ትለብሳለች ትምህርቷንም ትማራለች" በሚል መሪ ቃል በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፤ የሰልፉ ዓላማ፣ የአክሱም ከተማ ፍርድ ቤትና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ያሳለፉት ትዕዛዝና ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ለመጠየቅ መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል።

የምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ አደም አብዱልቃድር፤ "ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ለትምህርት ቢሮ እና ለአክሱም ትምህርት ጽህፈት ቤት ደብዳቤ ጻፍን ነገር ግን ምንም ለውጥ አላመጣም" ብለዋል፡፡

በአክሱም ከተማ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ የተፈፀመው ሕገወጥ በሆነ የሂጃብ ክልከላ ምክንያት፤ የእስልምና እምነት ተከታይ ሴት ተማሪዎች ለወራት ከትምህርት ገበታ እንዲገለሉ ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡

የትግራይ ትምህርት ቢሮ ጥር 8 ቀን ለአክሱም ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ፤ "መመሪያው ተጠናቆ ወደ ትምህርት ቤቶች እስኪወርድ ድረስ ከትምህርት ገበታ ውጪ ያሉ ተማሪዎች ከዕገዳው በፊት የነበረውን የአለባበስ ልብስ ለብሰው ወደ ትምህርት እንዲመለሱ" መወሰኑንም ምክር ቤቱ አስታውሷል፡፡

Post image

ነገር ግን ውሳኔው ተግባራዊ ባለመሆኑ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት "የፍርድ ቤት ውሳኔ እና የትምህርት ቢሮው ተግባራዊ እንዲሆን" የሚጠይቅ ሰልፍ እያደረገ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው፡፡

የሰልፉ ተሳታፊዎችም፤ ሂጃብ እንዲከበር፣ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እንዲሁም የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲከበር የሚጠይቁ በርካታ መፈክሮችን ይዘው ተስተውለዋል፡፡

Post image

ይህ ሰላማዊ ሰልፍ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና ከክልሉ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ዋና ፅህፈት ቤት መነሻውን በማድረግ በሮማናት አደባባይ ፍፃሜውን እንደሚያደርግ አሐዱ ከምክር ቤቱ ያገኘው መረጃ አመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ