ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው አትሌቶች መንደር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሆኑትን፤ አቶ ቢረሳው ምናለ ፈንታ በመግደል እና በማስገደል ወንጀል የተጠረጠሩትን ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ፖሊስ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ታሕሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ከምሽቱ 2:00 ሰዓት ከሥራ መልስ ወደ ቤታቸው በማምራት በራቸው ላይ ቆመው የመኪና ጥሩምባ እያሰሙ በር እስኪከፈትላቸው እየጠበቁ በነበረበት ወቅት ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ በተተኮሰባቸው ሦስት ጥይት ሕይወታቸው ማለፉን ገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት ፖሊስ የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ፤ ከወንጀሉ ጀርባ ያሉ ግለሰቦችን ማንነትና ምንነት ለመለየት ከአዲስ አበባ ሐዋሳ እስከ ሞያሌ ጫፍ የደረሰ መረጃና ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ተግባር ማከናወኑን አመላክቷል።
በዚህም ወንጀሉን በመፈፀም የተጠረጠረውን መኮንን ይዋል ይፍሩ የተባለውን ግለሰብ እና አብዩ አይተነው ፈንታ ጨምሮ፤ ለወንጀሉ መፈፀም አካባቢውን በመቆጣጠር ተሳትፎ የነበረውን አቶ ወርቁ መለሰ ካሴ የተባሉትን ሦስቱንም ተጠርጣሪዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በጌዴዎን ዞን ይርጋ ጨፌ ከተማ ላይ በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከወንጀሉ መፈፀም በፊት በተቀነባባረ ሴራ በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የግድያ ወንጀሉን የፈፀመው መኮንን ይዋል ይፍሩ የተባለው ግለሰብ በሕገ-ወጥ መንገድ በታጠቀው ማካሮቭ ሽጉጥ የአቶ አብዩ አይተነው ፈንታ የግል ጠባቂ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱ ተጠቁሟል።
ሁለቱ ግለሰቦች ከአቶ አብዩ አይተነው ፈንታ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት አንዱ የአካባቢውን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ለወንጀል ፈፃሚው ሁኔታውን ሲያመቻች መኮንን ይዋል ይፍሩ የተባለው ደግሞ፤ የግድያ ወንጀሉን መፈፀሙን ለፖሊስና ለፍርድ ቤት ከሰጡት የእምነት ቃል መረጋገጡ ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም በወንጀሉ ስፍራ የመርማሪዎችንና ዐቃቤ ሕግ ቡድን እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት የወንጀሉን አፈፃፀም መልሶ ማቋቋም (Re-construct) በተግባር ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡
በዕለቱም የወንጀሉ ፍሬ የሆነው ንብረትነቱ የአቶ አብዪ አይተነው ፈንታ የውግ ቁጥር የሌለው ማካሮቭ ሽጉጥ እና ለማምለጥ የሞከሩበት እንዲሁም ሽጉጡን የደበቁበት ላንድክሩዘር ተሽከርካሪ በኤግዚቢትነት መያዙም ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ማንነታቸውን በመቀየር ከወንጀሉ ተጠያቂነት ለማምለጥ በሐሰተኛ ሥም ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ ለመጥፋት መሞከራቸው የተገለጸም ሲሆን፤ ፖሊስ በሰራው የክትትልና የምርመራ ሥራ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተመላክቷል፡፡
በቀጣይም በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደረጉ የፍትህ ሂደቶች ውሳኔውን ተከታትሎ ለሕዝብ እንደሚያቀርብ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ