ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011” ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ማሰቡን አስታውቋል፡፡
ረቂቅ አዋጁን ለማሻሻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተካሄደ ውይይት፤ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ከአባላቶቻቸው ቁጥር ከ40 በመቶ በላይ፣ የክልል ፖርቲዎች ከአባላቶቻቸው ቁጥር ከ60 በመቶ በላይ የአንድ አካባቢ ወይም ብሔር ተወላጆች መሆን እንደማይገባቸው በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ መካተቱ ተነግሯል፡፡
አንድ ሀገር አቀፍ ፖርቲ ለመመስረት የሚጠበቀው አነስተኛ የአባላት ቁጥር 10 ሺሕ ሆኖ በነበረበት እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፤ "በፖርቲው አባልነት የሚካተቱ ሰዎች የአንድ አካባቢ ተወላጆች ግን ከ40 በመቶ መብለጥ አይኖሮበትም" ተብሏል።
አንድ የክልል ፖርቲም በተመሳሳይ መልኩ የአባላት ቁጥሩ 4 ሺሕ መሆን እንዳለበት የተቀመጠ ሲሆን፤ ከ60 በመቶ በላይ የአንድ አካባቢ ተወላጆች መሆን እንደሌለባቸው ተቀምጧል።
ሌላው አንድ ሀገራዊ ፖርቲ ከዚህ ቀደም የነበረው የክልል ስብጥር ከ5 ወደ 7 ክልሎች ከፍ የሚልበት አሰራር ረቂቁ መያዙም ተገልጿል።
ከማሻሻያዎቹ አንዱ አንደ አዲስ ፖርቲ ሲቋቋም ጊዜያዊ ፍቃድ እንዲሰጠው 3 ወር የነበረው ጊዜ ወደ 6 ወር ከፍ ያለ መሆኑም ተመላክቷል።
ይሁን እንጂ ማንኛውም ጊዜያዊ ፍቃድ የተሰጠው ፖርቲ መግለጫም ሆነ ቅስቀሳ ማድረግ እንደማይችልም ማሻሻያው ላይ በግልፅ ተቀምጧል።
ማሻሻያው ባካተታቸው የተለያዩ ጉዳይች ላይ ውይይት እየተደረገ ሲሆን፤ ለቀጣይ 7ኛ ዙር ምርጫ ግብዓት የሚሆኑ አሰራሮችም ይኖሩታል ተብሎ ይጠበቃል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ