መጋቢት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ላይ የሚገኘው የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በክልሎች የ'ይገባኛል' ጥያቄ ምክንያት የህልውና አደጋ እንደተጋረጠበት ተገልጿል፡፡
ፓርኩ ከአጎራባች አካባቢዎች የመጡ ከአንድ ሺሕ በላይ አባወራዎች ወደ ፓርኩ ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ገብተው በመስፈራቸው ምክንያት፤ 50 በመቶ የፓርኩ ይዞታ ከታቀደለት ዓላማ ውጭ እየሆነ ይገኛል ተብሏል፡፡
ሰፋሪዎቹ በተከለለው በፓርኩ ክፍል መኖሪያ ቤትና ትምህርት ቤቶችን ገንብተዋል፤ በሚያሰማሯቸው የግጦሽ እንስሳት አማካኝነትም ጥብቁን ደን እያወደሙ፣ እንስሳትን እያደኑ፣ እና ሌሎች የፓርኩን ሕልውና የሚፈታተኑ ተግባራት እየፈጸሙ በፓርኩ የተጠለሉ ብርቅዬ እንስሳት ላይ የመጥፋት አደጋ አንዲጋረጥ ማድረጋቸውን የጋሞ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን አስታውቋል።
የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ታከለ ሀሚሶ ፓርኩ በ1966 ዓ.ም. እንደተቋቋመ አስታውሰው፤ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን ይተዳደር እንደነበር ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"በፓርኩ ውድመት ቅሬታ የተነሳባቸው ሰፋሪዎች፤ ከ1983 ዓ.ም በኋላ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የፈለሱ ናቸው" ብለዋል፡፡
አክለውም በፓርኩ ውስጥ ያሉ እንደ ዜብራ ያሉ እንስሳትን ለማየት በፓርኩ ውስጥ በትንሹ 30 ደቂቃ መጓዝ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ "ይህ የሆነውም እንስሳት መኖሪያ ቤታቸውን ተቀምተው በመሸሻቸው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የመምሪያ ኃላፊው አቶ ታከለ የፓርኩን ነባር ወሰን ለማስጠበቅ፤ ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎችን በማስወጣት ሌላ አካባቢ ለማስፈርና እና ፓርኩን በአግባቡ ለማልማት ከኦሮሚያ ክልል ባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ቢፈረምም፤ ወደ ትግበራ አለመግባቱ ለሕገ-ወጥ ሰፋሪዎቹ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
አሐዱ የጋሞ ዞንን አቤቱታ በመያዝ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያን ስለ ጉዳዩ አነጋግሯል።
የመምሪያው ኃላፊ ዳዊት ዘለቀ በሰጡት ምላሽም፤ ወደ ፓርኩ የገቡ ሰፋሪዎች መኖራቸውን እንደማያውቁና ፓርኩ በክልሉ ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ከአጎራባች ክልሎች በሕገ-ወጥ መንገድ ገብተዋል የሚለው መረጃ ፈፅሞ የተሳሳተ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፤ "ነዋሪዎቹ የሚገኙትም በነባር ይዞታቸው እና በክልላቸው ነው" ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹን ወደ ሌሎ አካባቢዎች ለማስፈር የተካሄደ ስምምነት ስለመኖሩ እንደማያውቁም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አሐዱ በሁለቱ ክልሎች የ'ይገባኛል' ጥያቄ ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀውን የፓርኩን ህልውና ጉዳይ ለማጣራት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣንን ጠይቋል።
ፓርኩ በሁለቱ ክልሎች የሚገኝ መሆኑንና፣ ሕገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋና፣ አደን እየተካሄደበት እንደሚገኝ አምነው "የሚነሳበት የባለቤትነት ጥያቄ በጥናት ያልተረጋገጠ ነው" ሲሉ፤ የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ሰለሞን መኮንን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከምዕራብ ጉጂ ዞን ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ 'ቦታው የሰፋሪዎቱ ነባር ይዞታ ነው' የሚለው ግን የተሳሳተ መረጃ እንደሆነ አብራርተዋል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አያይዘውም ከዚህ በፊት በሁለቱም ወገን የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት የጋራ የምክክር መደረክ መዘጋጀቱን አስታውሰው፤ "ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመሰጠት እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ