መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የግልግል ዳኝነት ተቋማትን ለማቋቋምና ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመላኩ በፊት፤ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ሲሰሩ በቆዩ የውጭ ሀገር ድርጅቶች አስተያየት እንዲሰጡበት እየተደረገ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የግልግል ዳኝነት ማዕከላት ፈቃድ አሰጣጥ፣ ምዝገባ እና ቁጥጥርን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ከፍርድ ቤት፣ ከጠበቆች፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም፤ ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት ውይይት መካሄዱ ይታወሳል።

ረቂቅ ደንቡን ለማዘጋጀትም ባለፉት ዓመታት ሰፋ ያለ ጥናት ሲካሄድ መቆየቱን የገለጹት በሚኒስቴሩ የፍትሃብሔር ፍትህ አስተዳደር ዳይሬክተር ሄኖክ ተስፋዬ፤ በ2016 ዓ.ም በተደረገ የመጀመሪያ ውይይት ከባለሙያዎች የተሰጡ አስተያየቶችን በግብዓትነት በማካተት ተጨማሪ ጥናት በማድረግና በማሻሻል ረቂቅ ደንቡን ማዘጋጀት እንደታቸለ ተናግረዋል፡፡

ደንቡን ለማውጣት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ከጠበቆች፣ ዳኞች እና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችና ጥናቶች በማድረግ የተዘጋጀ ቢሆንም፤ ረቂቅ ደንቡ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመላኩ በፊት የመጨረሻ አስተያየቶች እየተሰበሰቡ ስለመሆኑ ነው ዳይሬክተሩ ለአሐዱ የተናገሩት።

አክለውም የግልግል ዳኝነትን በሚመለከት የቀረበው ረቂቅ ደንብ ከጸደቀ በኋላ፤ ጥያቄ ላቀረቡ ማህበራት እና ተቋማት የፍቃድ እና የምዝገባ ሂደቶች በቀጣይ እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

የረቂቅ ደንቡ ዋና አላማም ዓለም አቀፍ ጀረጃውን የጠበቀ ማዕከል እንዲኖር ማስቻል፣ ግልፅ መስፈርቶችን መደንገግና የግልግል ዳኝነት ማዕከላት ግልፅ የቁጥጥር ስርዓት መፍጠር መሆኑ በረቂቅ ደንቡ ተመላክቷል።

በተለይም የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የመሳሰሉ ጉዳዮችች ላይ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የተከራካሪ ወገኖችን ሕጋዊ መብትና ጥቅም በጠበቀ መልኩ ለመፍታት የሚያስችል አማራጭ የዳኝነት ሥርዓት መሆኑ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ